Monday, May 26, 2014

http://rogalandsavis.no/bilder/nyheter/nyhetbig/80226.jpg

የዞን ዘጠኙ በፍቃዱ፣ እንደ ሀገር ወዳድ ዜጋ… (ጋዜጠኛ ኤልያስ ገብሩ ጎዳና)

May 25, 2014


በመጋቢት ወር 2005 ዓ.ም ከጋዜጠኛ እና ጦማሪ በፍቃዱ ኃይሉ ጋር በአካል ለመጀመሪያ ጊዜ የተገናኘነው ዕንቁ መጽሔት ላይ ነበር እሱ ማኔጂንግ ኤዲተር እኔ ደግሞ ዋና አዘጋጅ ሆኜ፡፡ ከትውውቃችን ቀን ጀምሮ በፍቄ እንጂ በፍቃዱ ብየው እንኳን አላውቅም፡፡ በፍቃዱ ሳውቀው በጣም ረጋ ያለ፣ ትሁት፣ ሰውን በአክብሮት ብቻ የሚያናግር፣ አስተዋይ፣ ሰውን የሚረዳ፣ የራሱን ሀሳብ፣ አቋምና ዕምነት በቀላሉ የሚያስረዳ፣ የተለየ የሰዎችን ሀሳብ፣ አቋምና ዕምነት በጨዋ ደንብ የሚያከብር (ይሄን ዐይነት ባህሪ ብዙ ሰዎች ጋር መመልከት አልቻልኩም)፣ በሀሳቦች ላይ ውይይት የሚወድ፣ ጊዜውን በአግባቡ ከፋፍሎ ለሚወዳቸው ሥራዎቹ የሚሮጥ፣ ራሱን በዕውቀት፣ በወቅታዊ መረጃዎችና በተለያዩ ሥልጠናዎች ማበልጸግ የሚወድ እጅግ ቅን ልጅ ነው፡፡
በመጽሔቷ ላይ ለአምስት ወራት ያህል አብረን ሰርተን ነበር፡፡ በእነዚህ ጊዜያቶች ሀታታዊም ሆነ ግለ-ሃሳባዊ ጽሑፎችን ለማሰናዳት ጠቃሚ ወቅታዊ መረጃዎችን መሰብሰብ ይወዳል፡፡ በመረጃዎቹ ላይ ከባልደረቦቹ ጋር መደበኛም ሆነ መደበኛ ባልሆኑ ስብሳባዎች ላይ ውይይት ከፍቶ ሐሳቦችን መለዋወጥም ልምዱ ነበር፡፡ ይህን ዓይነት ልምድ ለየትኛውም ነጻ ጋዜጠኛ ወሳኝ ነው የሚል ጠንካራ እምነት አለኝ፡፡ በቢሮ ጠረጼዛ ላይ ተጀምረው በቢሮ ጠረጼዛ ላይ የሚጠናቀቁ ጽሑፎችን የሚያሰናዱ፣ ለመስክ ሥራ መልፋት የማይወዱ “ጋዜጠኞች” እና ጸሐፊያን በሀገራችን መኖራቸውንም አውቃለሁ፡፡
በፍቃዱ እና …ጭንቀቱ
የትኛውም የህትመት ውጤት በውስጡ ከሚይዛቸው የጽሑፍ ይዘቶች ባሻገር ለንባብ የሚሆን መስህብ ያለው የፊት ገጽ ግራፊክ ዲዛይን ማዘጋጀት ይጠበቅበታል፡፡ ግነት ባልበዛበት መልኩ የህትመቱን ወሳኝ ርዕሰ ጉዳይ እና ጉዳዮች የሚያሳይ ጥሩ የግራፊክ ዲዛይን በብዙ አንባቢያን ዘንድ ተወዳጅ መሆኑ አጠያያቂ አይመስለኝም፡፡
የሕትመት ውጤቶች የፊት ገጽ ግራፊክ ዲዛይን ከልብ ሲያስጨንቃቸው ከተመለከትኳቸው ጥቂት የሙያ አጋሮቼ መካከል አንዱ በፍቃዱ ነው፡፡ በተለያዩ የሥራ አጋጣሚዎች ከሀገር ውጭ ወጥቶ ሲመለስ፣ ሁሌ በጀርባው እና በትከሻው በሚያነግታት ቦርሳው ውስጥ የተለያዩ ሐገራትን መጽሔቶች እና ጋዜጦች ይይዝ ነበር – በፍቃዱ፡፡ እነዚህን የህትመት ውጤቶች ለእኛ ለባልደረቦቹ በኤዲቶሪያል ስብሰባ ወቅት እና መደበኛ ባልሆኑ ግንኙነቶች ወቅት ከቦርሳው አውጥቶ ስለጽሑፎች ይዘት፣ ስለሕትመት ጥራቶች፣ ስለፊት እና ውስጥ ገጾች ግራፊክ ዲዛይኖች የፈጠራ ጥበብ በተመሥጦ ለማስረዳት ሲሞክር ከልቡ ነው፡፡
ሰልፎች ላይ አጣሁት
በ2006 ዓ.ም በመዲናችን አዲስ አበባ አና በተለያዩ የክልል ከተሞች ከተመለከትናቸው ሁነቶች መካከል አንዱ ጥቂት ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያደረጉት እና ለማድረግ እየተንቀሳቀሱ የሚገኙት ሰላማዊ ሰልፍ ነው፡፡ይብዛም ይነስም በብዙ ውጣ ውረድ ተቃዋሚዎች የሚያደርጓቸው ሰላማዊ ሠልፎች እና ሰልፎችን ለማድረግ የሚያደርጓቸው እንቅስቃሴዎች እንደ ዜጋ ጥሩ ነው ብዬ አምናለሁ፡፡ ነገር ግን፣ ተቃዋሚ ፓርቲዎች የሚጠሯቸው ሰላማዊ ሰልፎች ሁሌም በሥርዓቱ ፈተና፣ ተግዳሮትና አፈና እንደገጠመው ነው፡፡ …
በፍቃዱን እንደኢትዮጵያዊ ዜጋ፣ ካከበርኩለት አቋሙ አንዱ የህዝብ ድምጾች በሚሰሙባቸው ሰላማዊ ሰልፎች ላይ በነቃ መንፈስ መገኘት መቻሉ፣ መታዘቡና ይህንንም በሕትመት እና በማኅበራዊ ሚዲያዎች ላይ መዘገብ መቻሉ ነው፡፡ (አንዳንድ ጋዜጠኞች እና ጸሐፊያን ተምኔታዊ የአብዮት ናፍቆትን በብዕራቸው ይከትባሉ፣ በስንት ትግል በሚገኙ ሰላማዊ ሰልፎች ላይ ግን ድርሽ ሲሉ አይታይም፡፡ ይህ ለእኔ ግምት ላይ የሚጥል ትልቅ ተቃርኖ ነው፡፡)
በቅርቡም ሰማያዊ እና አንድነት ፓርቲ በአዲስ አበባ ህዝብን ያማረሩ የማኅበራዊ አገልግሎት ችግሮች እንዲስተካከኩ በማለም የጠሯቸው ሰላማዊ ሰልፎች ነበሩ፡፡ በሁለቱም ሰልፎች ላይ ተገኝቻለሁ፡፡ ቀዳሚው ሰልፍ የነበረው የሰማያዊ ፓርቲ ነበር፡፡ በዚህ ቀን ግን በፍቃዱን በጣም አሰብኩት፡፡ ሰልፉ ላይ የለም! እዝነት ተሰማኝ፡፡ በፍቃዱ በዚህ ሰልፍ ላይ ተገኝቶ መዘገብ ያልቻለው ከሌሎች የሙያ አጋሮቹ ጋር እስከአሁን ድረስ ጥርት ብሎ ባልታወቀ የወንጀል ጉዳይ በፖሊስ ተጠርጥሮ በማዕከላዊ ወንጀል ምርመራ በመታሰሩ ምክንያት ነው፡፡
የፋሽስት ግራዚያኒ ሐውልት በጣሊያን መቆሙን ተከትሎ በባለዕራይ ወጣቶች ማኅበር አነሳሽነት እና በሰማያዊ ፓርቲ ድጋፍ በአምስት ኪሎ አደባባይ የሰማዕታት ሐውልት አካባቢ በተጠራው ሰልፍ ላይ ከተገኙት እና ለአንድ ቀን ያህል ለእስር ከተዳረጉት ሰዎች መካከል በፍቃዱ አንዱ ነበር፡፡ በፍቃዱ እንደሀገር ወዳድ ዜጋ፣ ጋዜጠኛና ጦማሪ ወቅታዊ ሀገራዊ ጉዳዮችን በትኩረት እንደሚከታተል እና ስለሀገር ጉዳይ ያገባኛል ብሎ ስለሚያስብ ይመስለኛል እንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ላይ የሚገኘው፡፡
ነፍሱ ወደየት ታደላለች?
በተፈጥሮ እያንዳንዳችን ለነፍሳችን ቅርብ የሆኑ ነገሮች አሉን፡፡ ከዚህ አኳያ በፍቃዱን ሳስበው ወደውስጤ ወዲያው የሚመጣልኝ አንድ ጉዳይ አለ፡፡ መጽሔቷ ሥራ ላይ በነበረው ቆይታ አስተውዬ ስመለከተው ነፍሱ ለማኅበራዊ ሚዲያ በጣም ቅርብ ሆና አይቻታለሁ፡፡
ሁላችንም የሥራ ባልደረቦች መጽሔቷን ለመዘጋጀት ሥራዎችን ተከፋፍለን እንሰራ ነበር፡፡ በተለይ ማተሚያ ቤት ለመግባት ሁለት ቀናት ሲቀሩ የሥራው ውጥረት ከፍ ያለ ነው፡፡ በፈቃዱም ከሚጽፋቸው ጽሑፎች ባሻገር ሌሎች ጽሑፎችን አርትዎት ያደርጋል፡፡ ሁሌም የሚገርመኝ ነገር፣ ጽሑፎች እየጻፈም ሆነ አርትኦት እያደረገ ሞባይሉን በመክፈት ማኅበራዊ ድረ-ገጾችን ወዲያው ወዲያው መከታተሉ ነበር፡፡ ይሄን ልምዱን በተደጋጋሚ ማየቴ ለብቻዬ ፈገግታን ይጭርብኝ ነበር፡፡ ለመጽሔቷ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ፍቃዱ ማሕተመወርቅ እና ለአዘጋጁ በሪሁን አዳነ ‹‹የበፍቄ ነፍስ ማኅበራዊ ሚዲያ ላይ ነች›› በማለት ፈገግታዬን አጋርቻቸው ነበር፡፡ እነሱም እየሳቁ ሃሳቤን መጋራታቸውን አስታውሳለሁ፡፡
የበፍቃዱን ብዕር በጥቂቱ
ዕንቁ ቁጥር 89፣ መጋቢት 2005 ዓ.ም ላይ ‹‹ግልጽ ደብዳቤ ለአቶ ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል እና አቶ በረከት ስምኦን›› በሚል ርዕስ የሀሳብን ነጻነት አደጋ ላይ መሆኑን በተመለከተ ጥሩ መጣጥፍ አስነብቦ ነበር፡፡ እንዲህ ቀነጨብኩት፡-
‹‹ከ20 ዓመታት በፊት ፓርቲዎቻችሁ ሕወሐትም ሆነ ብአዴን ብዙ የኢትዮጵያ ልጆች ሕይወታቸውን የገበሩለትን ጦርነት ያካሄዱት፣ ኢትዮጵያውያን ‹ጀርባቸውን ሳይመለከቱ› በነጻነት አመለካከታቸውን እና ሐሳባቸውን እንዲያንጸባርቁ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ብዙዎች ደማቸውን ያፈሰሱለት፣ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ የተሰየመለት (አንቀጽ 29)‹የአመለካከት እና ሐሳብን በነጻነት የመግለጽ መብት›ከኢትዮጵያውያን እጅ ቀስ በቀስ አፈትልኮ እየወጣ መሆኑ ቢያሳሳስበኝ ይህንን ግልጽ ደብዳቤ ለመጻፍ ተገደድኩ፡፡
…ክቡራን ሚኒስትሮች፣ መንግሥት የዜጎችን ሐሳቦች፣ ጋዜጦችንና ጦማሮችን በተደራጀ መልኩ እያሰሰ እና እያነበበ የሕዝቦችን ብሶት እና ችግር ተረድቶ ለመፍትሔው መረባረብ ሲኖርበት፣ ዜጎች መረጃዎቹን እንዳያወጡ እንቅፋት መሆንን ከመረጠ በየት በኩል ኃላፊነት የሚሰማው ማኅበረሰብ መፍጠር ይቻለዋል? መንግሥት በምሳሌነት የሚሳየውን ሥርዓት ከሕዝብ እንዴት መጠበቅ ይቻለዋል? እንግዲህ እነዚህን ጥያቄዎቼን በቅን ልቦና ተረድታችሁ ለጥያቄዎቼ ሁሉ መልስ እንደምትሰጡኝ በማመን በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 29 (2)ን በመጥቀስ ደብዳቤዬን እቋጫለሁ››
ለሥራ ጉዳይ ኬንያ ደርሶ ከተመለሰ በኋላ በቁጥር 94፣ ሰኔ 2005 ዓ.ም ላይ ደግሞ‹‹ናይሮቢን በአዲስ አበባ አይን›› በሚል ርዕስሥር እንዲህ ብሎ ነበር፡-Befekadu Zone9
‹‹ …ስለአዲስ አበባ እና ናይሮቢ ብዙ ማለት ይቻላል፡፡ ነገር ግን ገጹ አይበቃም፡፡ …ናይሮቢ በሌቦች እና አልፎ አልፎ በሽብር የምትታወክ ከተማ ስትሆን አዲስ አበባ ግን በአብዛኛው የጨዋታዎች እና ሰላማዊ የመሆኗ ነገር አስደሳች ነው፡፡ ችግሩ አዲስ አበባ ገና ፍዝዝ፣ ድንግዝ ያለች እና መነቃቃት የሚቀራት መሆኑ ነው፡፡›› ከዚህ ጽሑፍ በግልጽ ለመረዳት የቻልኩት በፍቃዱ ሽብር ሳይሆን ሰላም ወዳድ ኢትዮጵያዊ መሆኑን ነው፡፡
በሰኔ 2005 ዓ.ም፣ ቁጥር 93 ላይ፣‹‹የልማታችን ጥፋቶች›› በሚል ርዕስ የልማት አካሄዶችን በምክንያታዊነት እንዲህ በማለትም ተችቷል፡-

‹‹በቂ ጥናት ሳይደረግባቸው ወደተግባር የሚገባባቸው ሥራዎች የመንግሥትን ገንዘብ ሙሉ ለሙሉ ሊያከስሩ የሚችሉበት ዕድል አለ፡፡ …ግንባታዎችን ከማስጀመር እና ከማስጨረስ እኩል ለአገልግሎት የመዋላቸው ነገር ሊታሰብበት ይገባል፤ አለበለዚያ የልማት ሥራዎች ከላስቲክ ጀበናነት የበለጠ ትርጉም የሌላቸው ሊሆኑ ነው››
 ይህንን የበፍቃዱን የሀሳብ ድምዳሜ በግሌ የምጋራው ሃቅ ነው፡፡
በፍቃዱ (በፍቄ) መታሰርህ ብቻ ሳይሆን እጆችህ በካቴና ታስረው አራዳ ፍ/ቤት ሳይህ ጥልቅ ሀዘን ቢሰማኝም ጠመንጃ በወደሩ ፖሊሶች መካከል ከአንተ ያየሁት የፈገግታ ብልጭታ መንፈሰ ጠንካራነትህን አሰይቶኛል፡፡ አይዞን! እውነት ታሸንፋለች፡፡
source ECADF

Wednesday, May 14, 2014

የወያኔን ውድቀትና የኢትዮጵያን ትንሣኤ ለማፋጠን ኅብረታችን ይጠንክር! (ግንቦት7)

May 9, 2014
Ginbot 7 weekly editorialግንቦት 7፡ የፍትህ፣ የነፃነትና ዲሞክራሲ ንቅናቄ፣ በግፍ ሕይወታቸውን ባጡ ዜጎች መርዶ የተሰማውን ጥልቅ ሀዘን እና ቁጭት ይገልፃል፤ ለቤተሰቦቻቸውም መጽናናትን ይመኛል። ህወሓት እና አጋፋሪው ኦህዴድ በነዙት ሽብር ሳቢያ የአካል ጉዳት የደረሰባችሁ፣ የተደበደባችሁ እና ለእስር የተዳረጋችሁ ወገኖቻችንም ህመማችሁም እስራችሁም የሁላችንም ነው። መላው ኢትዮጵያዊ ወገናችሁ ከእናንተ ጋር ተገድሏል፣ ቆስሏል፣ ተደብድቧል፣ ተግዟል፣ ታስሯል። ህወሓት፣ ኦህዴድ እና በዚህ ጭፍጨፋ እጃቸው ያለበት ሁሉ ከተጠያቂነት የማያመልጡ መሆኑን ግንቦት 7 ደጋግሞ ያስገነዝባል።
በህወሓት ዘረኛና ፋሽስታዊ አገዛዝ ያልተበደለ የኢትዮጵያ ክፍል የለም። የወያኔ አጋፋሪ የሆነው አህዴድ የኦሮሞ ወጣቶችን፣ ሕፃናትንና አዛውንትን ሲጨፈጭፍና ሲያስጨፈጭፍ፣ ሌላው አጋፋሪ ብአዴን ደግሞ በጎንደርና አካባቢው ተመሳሳይ ጭፍጨፋዎችን አካሂዷል። ወያኔ ከፋሺስት ኢጣልያ ወርሶ ለሃያ ዓመታት በትጋት ያራመደው “የከፋፍለህ ግዛ” ፓሊሲ ምርት እነሆ ዛሬ በዓይኖቻችን እያየን ነው። ፋሽስት ጣልያን ጀምሮት የነበረውን ኢትዮጵያን የማጥፋት ስትራቴጄ ለማጠናቀቅ ህወሓት በጥድፊያ ላይ ነው። ይህን እኩይ ዓላማ ማስቆም የሁላችን ኃላፊነት ነው።
የመከላከያ ሠራዊት እና የፊደራል ፓሊስ አባላት ሆይ፣ ለዘረኛው ወያኔ መሣሪያ ሆናችሁ ወገናችሁን አትፍጁ! እናንተ የምታገለግሉት ሥርዓት፣ ከእናንተ መካከል ኦሮሞ ያልሆኑትን እየመረጠ ኦሮሞዎች ወገኖቻችንን እንዲገሉ፣ አማራ ያልሆኑት ተመርጠው አማሮችን እንዲገሉ የሚልክ መሠሪ መሆኑን የምታውቁት ነው። ወያኔ አንዳችንን በሌላችችን ላይ እያዘመተ እርስ በርስ ሊያፋጀን ቆርጦ መነሳቱን አስተውሉ። ይህን እኩይ ዓላማ የማክሸፍ ሥራ የናንተም ኃላፊነት እንደሆነ ግንቦት 7 ያስገነዝባል።
በወያኔ የስለላ መዋቅር ውስጥ ያላችሁ ህሊና ያላችሁ ኢትዮጵያዊያን ወገኖቻችን የምትሠሩት ሥራ አገራችን ወደየት ሊወስዳት እንደሚችል ቆም ብላችሁ አስተውሉ። እናንተ ዛሬ የምትወስዱት ቆራጥ እርምጃ የበርካታ ሕዝብ ሕይወት ሊታደርግ ይችላል።
የኢትዮጵያ ወጣቶች በተለይም የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ተከፋፍላችሁው ወያኔን መቃወም የትም አያደርስም። በኦሮሞው መገደል አማራው፣ ትግሬው፣ ወላይታው፣ ጉራጌው ካላመመው፤ አማራው ሲበደል ኦሮሞውና ሌላው እንዲያመው እንዴት መጠበቅ ይቻላል። እናንት ወጣቶች ከዘውግ ቆጠራ በላይ ሁኑ። ዛሬ የሚደረጉ ትናንሽ ነገሮች እንኳን የረዥም የወደፊት ውጤት እንዳላቸው ተገንዘቡ። የወደፊቷ ኢትዮጵያ የእናንተ ናት፤ የምትመኟችን ከራሷ ጋር የታረቀች ኢትዮጵያን ለመፍጠር በቅድሚያ እናንተ መታረቅ ይኖርባችኋል። የሁላችንም ቀንደኛ ጠላት ወያኔ ነው ትኩረታችሁን እሱ ላይ አድርጉ።
ውድ የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ!!!! አውቀውም ሆነ ሳያውቁ በወያኔ ዘረኛ ፕሮፖጋንዳ ተጠልፈው በንግግራቸው ሕዝብን ከሕዝብ ጋር የሚያቃቅሩ ሰዎችን አትስማ። የመረረ፣ የሚያስቆጣ ንግግር እንኳን ቢናገሩ ንቀህ ተዋቸው። በወያኔ ውስጥም ሆነ ከወያኔ ውጭ ሆነው ብሔርና ዘርን እያነሱ ተማረው ማስመረር የሚሹ ሁሉ ግባቸው አንድ ነው። በየትኛውም ወገን ቢሆኑ እነሱ የጥፋት ኃይሎች ናቸው፤ እነሱ የኢትዮጵያና የሕዝቧ ጠላት የሆነው የህወሓት መጠቀሚያ ናቸው።
በአሁኑ ሰዓት የኢትዮጵያ ሕዝብ ጠላት ህወሓት እና ህወሓት የዘረጋው ሥርዓት ነው። የጋራ ትኩረታችን በጋራ ጠላታችን ላይ ብቻ ይሁን። ወያኔ ትኩረታችን ለመበተን ብዙ ነገሮችን ይጀምር ይሆናል፤ እርስ በራሳችን ከማባላትም አልፎ ጎረቤቶቻችንን መጎነታተል ይጀምር ይሆናል። በእንዲህ ዓይነት ድርጊት ትኩረታችን መበተን ፈጽሞ የለበትም።
እኛ ኅብረታችንን ስናጠናክር የተዳከመው ወያኔ ይበልጥ ይዳከማል። ሊበታትኑን የዳከሩትን አሳፍረን ኅብረታችን እናጠነክራለን። ይህ ደግሞ የወያኔ ውድቀት እና የኢትዮጵያ ትንሣኤን ያፋጥናል።
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!!
source ECADF

Tuesday, May 13, 2014

የሃይለመድህን አበራ ጉዳይ

ዶ/ር ሼክስፒር ፈይሳ የሃይለመድህን አበራን ጉዳይ ለመከታተል ወደ ጄኔቫ አመራ


13 may 2014 (EMF ) የኢትዮጵያ አየር መንገድ ረዳት ፓይለት ሃይለመድህን አበራን ጉዳይ ለመከታተል ኢትዮጵያዊው የህግ ባለሞያ ዶ/ር ሼክስፒር ፈይሳ ባለፈው ሳምንት ወደ ጄኔቭ-ስዊዘርላንድ ተጉዟል።
Ethiopian lawyer Shakespear Feyissa in Switzerland
ዶ/ር ሼክስፒር ፈይሳ ጄኔቭ-ስዊዘርላንድ
ሼክስፒር ፈይሳ የረዳት ፓይለቱን ጉዳይ ከሚኖርበት ከሲያትል ከተማ በቅርብ ሲከታተል ቆይቶ ነው ወደ ጄኔቭ ያመራው። ጄኔቭ እንደደረሰም የሃይለመድህን አበራን ጠበቃና ጉዳዩን ከሚከታተሉ አካላት ጋር በስፋት ተወያይቷል። በተለይ ከረዳት ፓይለቱ ጠበቃ ጋር ረጅም ሰዓታት በመውሰድ በበርካታ የህግና የቴክኒክ ጉዳዮች ላይ በጥልቅ ተነጋግሯል።
ረዳት ፓይለቱ ሙሉ በሙሉ ጤነኛ እንደሆነም ለማወቅ ተችሏል።
ኢትዮጵያዊ የህግና እንዳስፈለጊነቱ የህክምና ባለሞያዎች ጋር እንዲገናኝም ዶ/ር ሼክስፒር ምክር ሰጥቷል።
የረዳት ፓይለቱ ጠበቃ የስዊስ መንግስት ሃይለመድህን አበራን ለኢትዮጵያ አሳልፎ እንደማይሰጥና ግዚያዊ የስደት ፈቃድ እንዲሰጠው ውሳኔ መተላለፉን ያረጋገጠ ሲሆን – ጉዳዩ በቅርብ ጊዜ በሚሰየመው ግልጽ ችሎት እልባት እንደሚያገኝ አመላክቷል።
የሃይለመድህን አበራን ወደ ኢትዮጵያ ለማስመለስ በአቶ አስመላሽ ወልደ-ስላሴ የተመራ ከፍተኛ የኢህአዴግ ቡድን ጄኔቭ፣ ከርሞ ጥያቄው በስዊዘርላንድ መንግስት ውድቅ መደረጉ ይታወሳል።
ቡድኑ የስዊስ ፌዴሬሽን የህግ አካላትን ለማሳመን ካቀረበው ምክንያት ዋነኛው፣ ረዳት ፓይለት ሃይለመድህን አበራ የአእምሮ በሽተኛ መሆኑን እና ይህንንም የራሱ ቤተሰብ አባላት እንዳረጋገጡላቸው ገልጸዋል። የስዊዝ መንግስት ግን ጥያቄውን ውድቅ አድርጎታል። ለዚህም የሰጠው ዋነኛ ምክንያት፤ የሞት ፍርድን ተግባራዊ ለሚያደርግ መንግስት ማንንም አሳልፌ አልሰጥም የሚል ሲሆን ይህ ባይሆንም፣ በስዊዘርላንድ እና በኢትዮጵያ መሃል ተጠርጣሪ እስረኛን የማስመለስ ውል የለም ብለዋል።Ethiopian lawyer Shakespear Feyissa
ረዳት ፓይለቱ ለግዜው ሰው ማግኘት እንደማይፈልግ የተነገረ ሲሆን: ወንድሙ ዶ/ር እንዳላማው አበራ እና በጀርመን የምትኖር እህቱ ሃይማኖት አበራ ጄኔቭ ድረስ በመሄድ ሃይለመድህን አበራን ከሚገኝበት እስር ቤት ጎብኝተውታል።
ወጣት ሃይለመድህን አበራ ባለፈው የካቲት 10፣ 2006 ዓ.ም. የኢትዮጵያ አየር መንገድ ንብረት የሆነውን ቦይንግ 767 አግቶ ጄኔቭ ስዊዘርላንድ ላይ በማሳረፍ እዚያው የፖለቲካ ጥገኝነት መጠየቁ ይታወሳል። የአለም ዜና ርዕስ ሁሉ ትኩረት ስቦ የነበረው ይህ ልዩ ክስተት የኢትዮጵያን የሰብአዊ መብት ሁኔታና የአስተዳደር በደል አደባባይ በማውጣቱ የገዢው ፓርቲ አባላትን እጅግ እንዳበሳጨ ይነገራል።
አንዳንድ መገናኘ ብዙሃን እንደገለጹት የአጎቱ ድንገተኛ ህልፈት ርዳት ፓይለቱን አስቆጥቶት ነበር። የሃይለመድህን አበራ አጎት፤ ዶ/ር እምሩ ሥዩም ህይወት በድንገት ማለፍ ለብዙዎች ያልተፈታ እንቆቅልሽ ነው። ዶ/ር እምሩ ሥዩም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር ነበሩ።
በአለም ዙሪያ ያሉ ኢትዮጵያውያን ወጣቱ ፓይለት ሃይለመድህን አበራን መደገፋቸውን እንደቀጠሉ ሲሆን በረዳት ፓይለቱ ስም የተከፈቱ ድረ-ገጾች እና የፌስቡክ መድረኮች ላይ አሁንም ሰፊ ዘመቻ በማድረግ ላይ ይገኛሉ።
ዶ/ር ሼክስፒር ፈይሳ በረዳቱ ጉዳይ ላይ ማንኛውንም ትብብር ለማድረግ ቃል የገባ ሲሆን የስዊስ ጠበቆችም በዚህ ከክፍያ ነጸ የሆነ ትብብሩ አድናቆታቸውን ገልጸዋል።
SOURCE ECADF