Wednesday, February 18, 2015

አቶ አሰፋ ጫቦን ለቀቅ… ከሺመልስ አበበ

  • 222
     
    Share
አቶ አሰፋ ጫቦ
አቶ አሰፋ ጫቦ
አቶ አሰፋ ጫቦ በኢሳት ቴሌቪዥን፣ በአዉራምባ ታይምስ ድህረ ገጽና በፊንፊኔ የድህረ ገጽ ሬድዮ ያደረጉትን ቃለ መጠይቆች ተመልክቻለሁ፤ አድምጫለሁ። እንዲሁም በኢትዮሚዲያ ድህረ ገጽ ላይ በብእር ስሙ መላኩ ይስማዉ የሚባል ግለሰብ የጻፈዉን ዉርጅብኝ አንብቤ በጣም ከልቤ አዘንኩ። በፍኖት ሬድዮም ስለ አቶ አሰፋ የተለፈፈዉን ተራ ትችትና ዘለፋም ሰምቼ በጣም አዘንኩ። አቶ አሰፋ የተናገሩትን በመረጃም ሆነ በሙግት መልክ በሰለጠነ መንገድ አንድ በአንድ መሻር ሲቻል ከደረጃ ዝቅ ባለ መንገድ ተራ ትችት ዉስጥ መግባቱ ከግምት ያስገባል እንጂ ሌላ እዉቀት የሚጨምር አይደለም። ለመሆኑ መቼ ነዉ የሰለጠነ ዉይይት የሚደረገዉ?
ይህ አይነቱ ስም የመጥራትና አወቅሁሽ ናቁሽ ትችት በቀድሞዉ ቀዝቃዛ ጦርነት ጊዜ ሲካሄድ የነበረ ባህርይ በአሁኑ ወቅት እተካሄደ ማየቱ ምን ያህል ሗላቀር የፖለቲካ ባህርይ እንደሆነ መረዳት አያዳግትም። በደርግ ጊዜ የነበረን የፖለቲካ ቆርሾ በአሁኑ ሰአት እንዳለ መድገም ደግሞ መለወጥ አለመቻልን የሚያመለክት ይመስለኛል። በአቶ አሰፋ ላይ የተካሄደዉ አግባብ የሌለዉ ትችት ይህንን መልስ እንድሰጥ አስገድዶኛል።
እኔ አቶ አሰፋ ጫቦን አዉቃቸዋለሁ። በመጀመሪያ ያወቅሗቸዉ የጋርዱላ አዉራጃ አስተዳዳሪ ሆነዉ ጊዶሌ ከተማ ሲመጡ ነዉ።
በየካቲት ስድሳ ስድስት አመተ ምህረት ንቅናቄ አርባ ምንጭ መጥተዉ ከሼቻ (የላይኛዉ ከተማ) ወደ ሲቀላ (የታችኛዉ ከተማ) ይነዱ በነበሩት ጉርድ ላንድሮቨር ከሌሎች ተማሪዎች ጋር ሆኜ ወስደዉናል። በፈገግታ ላንድሮቨሩን አቁመዉ ግቡ ብለዉን ስለለዉጡ እያወሩንና እኛም ደግሞ በአንክሮ እያዳመጥን እንደነበር አስታዉሳለሁ። ደርግ ስልጣን ላይ ወጥቶ እድገት በህብረትን አዉጆ እኔም ደግሞ ከአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወደ ከምባ ወረዳ ከአዲስ አበባ ከመጡ ዘማቾች ጋር ዘመትኩ። ታናሽ ወንድማቸዉ የሆነዉ እሸቱ ጫቦም እንዲሁ ዘምቶ ነበር።
ዘመቻዉን ጥዬ ስመለስ አቶ አሰፋ የህዝብ ድርጅት ጉዳይ ጊዚያዊ ጽህፈት ቤት ዋና ጸሀፊ ሆነዉ እንደተሾሙ አርባ ምንጭ ከተማ ሰማሁ። ይህ መስሪያ ቤት ካድሬዎችን ቀጥሮ በየቦታዉ እየላከ ቅስቀሳ የሚያስደርግ መስሪያ ቤት እንደሆነም በወቅቱ ተረዳሁ። በወቅቱ በነበረኝ ንቃተ ህሊናና ከጓደኖቸም ካገኘሁት ምክር ከአቶ አሰፋ መራቁ የተሻለ ነዉ የሚል እምነት አሳድሮብኝ ነበር።እ. ኢ. አ. በ1969 ዓ. ም. ትምህርት ጀመርን። በኢሕአፓ እና በመኢሶን መካከል ይካረር ነበረዉ የፖለቲካ ትግል በአርባ ምንጭ ከተማና በነበርኩትም ትምህርት ቤትም ይብላላ ነበር።
እ. ኢ. አ. በ1969 ዓ. ም. በአንድ ወቅት የአርባ ምንጭ አጠቃላይ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት መማሪያ ክፍሎች ዴስኮች ላይ ለእያንዳንዱ ተማሪ ተብሎ በእጅ የተጻፉ የኢሕአፓ ወረቀቶች ተበትነዉ ነበር። ክፍል ስገባ ወረቀቱን አነበብኩ። ወረቀቱ የተሞላዉ በኢህአፓ መፈክሮች ነዉ። እያንዳንዱም ተማሪ አንብቦት ዝም ብሏል። ትምህርትም ተጀምሮ ሳለ የአርባ ምንጭ ወረዳ ፖሊስ ጣቢአ አዛዥ የነበረ ሻምበል ተስፋዬ የሚባል ከጠቋሚ ተማሪዎች ጋር በመሆን በየክፍሉ እየዞረ ማን ነዉ ወረቀት የበተነዉ እያለ ይጮህ ነበር።እኔ የነበርኩበት ክፍልም መጥቶ ጮኸብን። ብዙ ተማሪዎች ክፍል ለቅቀዉ ሲወጡ እኛም ወጣን። ብዙ ጠቋሚ ተማሪዎች በቦክስ ተመቱ። ቁጥሩ አንድ መቶ የሚሆን ማስ የሚባል (ፈረንሳይ የተሰራ አስር ጥይት ጎራሽ) ግማሽ አዉቶማቲክ ጠብመንጃ የታጠቀ የፈጥኖ ደራሽ ሀይል ትምህርት ቤቱን ከበበ። በዚህን ጊዜ ነበር አቶ አሰፋ ጫቦ ወደ ትምህርት ቤታችን የመጡት።
አቶ አሰፋ በጉርድ ላንድሮቨር ሲመጡ ተማሪዎች አሰገቧቸዉ ብለዉ ሲጮሁ ዋና መግቢያዉን በር ይጠብቁ የነበሩት ተማሪዎች አስገቧቸዉ። ከዚያም ሰንደቅ አላማ የሚከበርበት ቦታ መኪናዉን አቁመዉ ከመኪና ሲወጡ ተማሪዎች ከበቧቸዉ። ከዚያም ተማሪዎች ጪኸታቸዉን ማሰማት ጀመሩ። አቶ አሰፋ የላንድሮቨሩ ሞተር ኮፈን ላይ ቆመዉ ሳለ የድምጽ ማጉያ ተሰጥቶአቸዉ ከተማሪዎች ጥያቄ መቀበል ጀመሩ። ከዚያም መልስ መስጠት ጀመሩ። ተማሪዎች በጥሞና አዳመጧቸዉ። እርሳቸዉም “…ይህቺ የዴሞ ቅስቀሳ ነች። ትምህርታችሁን ብትከታተሉ ይበልጥ ትጠቀማላችሁ…” ብለዉ ተናገሩ። ሌሎች መልሶችም ባያረኩን እንኳ እሳቸዉ ምልስ ሊሰጡ እንደማይችሉ ተማሪዎች የተረዱትም ይመስለኛል። በቦክስ የተመቱና የደሙ ተማሪዎች በአምቡላንስ ወደ ሆሲፒታል ተላኩ። ጥቃቱን የፈጸሙ ተማሪዎች ከተጠያቂነት እንደማይድኑ አቶ አሰፋ ማሳሰቢያ ሰጡ። ይህ እየሆነ ሳለ የመቶ አለቃ ጳዉሎስ ቦጋለ መጥቶ አቶ አሰፋ እንዲናገር እድል ሲሰጠዉ ድምጽ ማጉያዉን ተቀበሎ መደንፋት ጀመረ። “…የአድሀሪያን ልጆች የሬሳ ሳጥን በሚያክል አገልግል ፍትፍትና ጭኮ እየተላከላቸዉ ተንደላቅቀዉ እየተማሩ የጭቁን ልጆች እንዳይማሩ ለማድረግ የተጠነሰሰ ሴራ ነዉ…” እያለ ደነፋ። ብዙ ዛቻዎችንም ዛተ። ከዚያም አቶ አሰፋ ከመቶ አለቃ ጳዉሎስ ጋር ለጥቂት ደቂቃዎች ተነጋገረ። የመቶ አለቃ ጳዉሎስ እየተቆጨ ሲናገር እንደነበር ታዘብኩ። ኮሎኔል ተስፋዬ የሚባል የፈጥኖ ደራሽ ሀይሉን መርቶ የመጣዉ ወደነርሱ ጠጋ ብሎ የነገሩትን ሰምቶ ሄደ። ከዚያም አቶ አሰፋ ለዚያኑ ቀን ትምህርት እንደሌለና ወደ ቤታችን እንድንሄድ ነገሩን። እኛም ወደ ቤት ስንሄድ የታዘብኩት ነገር ቢኖር የመቶ አለቃ ጳዉሎስ ቦጋለ ከአቶ አሰፋ ጋር ሲጨቃጨቅ እንደነበር ነዉ። በወቅቱ ከጓደኞቼ ጋር ስንነጋገር የደረስንበት መደምደሚያ ቢኖር የመቶ አለቃ ጳዉሎስ እርምጃ ለመዉሰድ ፈልጎ በአቶ አሰፋ እምቢተኝነትና ተጽእኖ ደም ላይፈስ እንዳልቻለ ነዉ። በወቅቱ ቁጥሩ አንድ መቶ የሚሆነዉ የፈጥኖ ደራሽ ሀይል የግድያ ትእዛዝ ቢሰጠዉ ኖሮ ምን ያህል ተማሪ እንደሚሞት መገመት አያዳግትም.። በተማሪዎችም ዘንድ አቶ አሰፋ ክብር ሊያገኙም ችለዋል ይህችን ዉለታ ለተማሪዎች ስለዋሉ።
ከአቶ አሰፋ ጋር በርእዮተ አለም አመለካከት ብለያይም አንኳ በእርሳቸዉ ብርታት ከሞት ልድን ችያለሁ። በወቅቱ ከከበቡን ፈጥኖ ደራሾች ቢያንስ ወደ አስር የሚሆኑትን አዉቃቸዋለሁ። ተማሪዎች የነበሩ ናቸዉ። በሌላ ወቅት አግኝቼ ስጠይቃቸዉ በአቶ አሰፋ እምቢተኝነት የመቶ አለቃ ጳዉሎስ ቦጋለ ትእዛዝ ለመስጠት እንዳልፈለገ አዛዣቸዉ የነበረዉ ኮሎኔል ተስፋዬ እንደነገራቸዉ አጫወቱኝ። ትእዛዝ ቢሰጣቸዉ ኖሮ እኔንም ሊገድሉ እንደሚችሉ ነገሩኝ። እኔም የህችን የአቶ አሰፋን ዉለታ ሁል ጊዜ እንዳስታዉስ አደረገኝ። አቶ አሰፋን ወድጄ አላዉቅም። ግን ይህ ዉለታቸዉ እንዳከብራቸዉ አድሮጎኛል።
ብዙ ሰዎችን አስገድለዋል የሚል ክስና ስሞታ በተደረጉት ትችቶች ዉስጥ ተካትተዋል። አርባ ምንጭ ዉስጥ የተደረጉት ግርፊያዎች ናቸዉ የኢሕአፓን አባላትና ደጋፊዎች ለማጋለጥ ተብሎ። ፋሺስቱ አሊ ሙሳ በገዛ እጁ የገደላቸዉ አተ ተፈሪ (የእኔ ዘመድ የሆነችዉ አየለች ማመጫ ባለቤት)፣ ክፈተዉ (የአጎቴ ባለቤት ወንድም)፣ እና ኑሩ (አቶ አሰፋ ሲታሰሩ በእርሳቸዉ ምትክ የተመደበዉ) ሲሆኑ አርባ ምንጭ ዉስጥ ምንም የፖለቲካ ግድያ አልተካሄደም። አንድም የኢሕአፓ አባል አልተገደለም። ግርፋት ግን ተካሂዷል። በጎፋ አዉራጃ ዋና ከተማ ሳዉላ ከተማ የመቶ አለቃ ጳዉሎስ ቦጋለ ፊዉዳሎች ናቸዉ ብሎ የረሸናቸዉ ጥቂት ግለሰቦች ናቸዉ። የገለብና ሀመር ባኮ አዉራጃ ዋና ከተማ ዉስጥ አንድ የጊዶሌ ተወላጅ የሆነ ካድሬ አንድ ነጋዴ ገድሏል። እ. ኢ. አ. በነሐሴ ወር 1976 ዓ. ም. (August 1984 G. C.) ለትምህርት ኢትዮጵያን ለቅቄ እስከምወጣ ድረስ እዚያዉ ጋሞ ጎፋ የኖርኩ ስለሆነ ሁኔታዎችን ጠንቅቄ አዉቃለሁ። በአቶ አሰፋ ላይ የተደረገዉ አሳዛኝ ትችት ከእዉነት የራቀ መሆኑ በጣም አሳዘነኝ። ጸሀፊዎቹና ተቺዎቹ ከተባራሪ ወሬ የቀሰሙትን ነገር እንደ እዉነታ አድርገዉ ማቅረባቸዉ ዋጋ ቢስነቱን ከማጋለጥ በስተቀር የሚያመጣዉ ነገር ያለ አይመስለኝም። አቶ አሰፋ ቢጠየቁም እንኳ በኢሕአፓነት ተጠርጥረዉና ታስረዉ ለተገረፉት እንጂ በአስገዳይነት አይደለም። ብዙ ተማሪዎች በኢሕአፓነት ተጠርጥረዉ በተለያዩ ቦታዎች ታስረዉና ተገርፈዉ ወደ ሰላማዊ ኑሮና ትምህርት እንዲመለሱ ተደርጓል። ግድያ እንዳይካሄድ ካድሬዎች እንኳ አቶ አሰፋን ያሙ የነበረ ለመሆኑ ሲነገር ሰምቻለሁ። አቶ አሰፋ ኢሕአፓዎች እንዳይገደሉ አድርገዋል። ጋሞ ጎፋ ዉስጥ ባጠቃላይ እስራትና ግርፊያ ተካሄደ እንጂ የፖለቲካ ግድያ አልተካሄደም። ይህ ደግሞ በአዲሰ አበባና ሌሎች ከተሞች አንዳንድ የቀበሌ ሊቀመናብርት በቀይ ሽብር ወቅት ወጣቶች እንዳይገደሉባቸዉ ያስሯቸዉና ይገርፏቸዉ ከነበረዉ በምንም ተአምር አይለይም።
ኢሕአፓዎች ያደረጉትስ የከተማ ቃፊር የግድያ ዘመቻ እና በመካከላቸዉ በነበረዉ የፖለቲካ መከፋፈል እርስ በእርስ የተጋደሉት፤ እንዲሁም ወጣቱን ያስጨረሱት ተረሳና የአቶ አሰፋ ድርጊት ጎልቶ ታይቶ ነዉ ወይ እንዲህ አይነቱ ትችት የተደረገዉ? ትችት በትክክል መረጃ ተይዞ ሲቀርብ ያምራል። ያለበለዚያ ቂም መወጣጫ ወይም ለፖለቲካ ፍጆታ ይዉላል። ደርግም፣ ኢሕአፓም፣ መኢሶንም፣ ወያኔም ሆን ማንም ድርጅትም ሆነ ግለሰብ ከተጠያቂነት አይድንም።
ኢትዮጵያ ለሁላችንም እኩል እናት አገር ነች። ማንም ከማንም አይበልጥም። የበደሏት፣ የገደሏትና የሞቱላትም እንዲሁ አሉ። እያንዳንዱ ትዉልድ የራሱ የሆነ ባህርይ እንዳለዉ ሁሉ ለቀጣዩ ትዉልድ የሚያስተላልፈዉ ትምህርት ገንቢ ሀሳብና ራእይ ያለዉ ቢሆን ይመረጣል። ካልሆነም ደግሞ የታሪክ ተወቃሽ ሆኖ ይቀራል። አገር በቂም በቀል የሚመራ መሆን የለበትም። ታሪክም ቢሆን የሚጻፈዉ በቂም በቀል አይደለም። ወቀሳ፣ ትችትና ሂስ ገንቢ የሚሆኑት አግባብ ባለዉ ሁኔታ ሲፈጸሙ ነዉ። ታሪክም እንዳይወቅሰን ደግሞ ብናስብበት የበለጠ ጠቃሚነት አለዉ ብዬ አምናለሁ።
ሺመልስ አበበ
shimelisabebe@gmail.com
SOURCE ZEHABESHA 

Thursday, January 22, 2015

“ጋዜጠኝነት ወንጀል አይደለም” – በኢትዮጵያ የመገናኛ-ብዙሃን ነጻነት ላይ የሚፈፀም የመብት ጥሰት (የሂውማን ራይትስ ዋች መግለጫ)

  • 2
     
    Share
Jail
እ.ኤ.አ. ጃንዋሪ 2015 ዓ.ም. ማጠቃለያ
የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) እ.ኤ.አ. በ2010 ዓ.ም. በተካሄደው ምርጫ 99.6 በመቶ የፓርላማ መቀመጫን ካሸነፈ ጊዜ ጀምሮ የኢትዮጵያ መንግስት ሃሳብን የመግለጽ ነጻነትን እና መረጃ የማግኘት መብትን በመገደብ በግል መገናኛ-ብዙሃን ላይ እያሳደረ ያለውን አሉታዊ ተጽዕኖ አባብሶታል፡፡ እ.ኤ.አ. ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ቢያንስ 60 ጋዜጠኞች ሃገር ለቀው የተሰደዱ ሲሆን ሌሎች 19 ጋዜጠኞች ደግሞ በእስር ላይ እየተሰቃዩ ይገኛሉ፡፡ መንግስት በደርዘኖች የሚቆጠሩ ህትመቶችን ዘግቷል፤ እንዲሁም አብዛኛዎቹን የቴሌቪዥን እና የሬድዮ ስርጭቶች በቁጥጥሩ ስር በማድረግ ኢትዮጵየዊያን የሀገር ውስጥ የፖለቲካ ጉዳዮችን በተመለከተ ነጻ መረጃ እና ትንታኔ የሚያገኙበትን እድል አጣቧል። በግንቦት 2007 በሚካሄደው ምርጫ መገናኛ-ብዙሃኑ ህዝቡን በወሳኝ ጉዳዮች ላይ በማስተማርም ሆነ መረጃ በመስጠት ረገድ ቁልፍ ሚና ሊጫወቱ ይችሉ ነበር፤ እንዲሁም የመከራከሪያ መድረክ በመሆን ሊያገለግሉ ይችሉ ነበር፤ ይሁን እንጂ መንግስት በሃገሪቱ ላለው ብቸኛ የበላይነት የግሉን መገናኛ-ብዙሃን እንደ ስጋት አድርጎ በመውሰድ የግሉን መገናኛ-ብዙሃን፣ ነጻ ጋዜተኝነትን እና ተቺ ትንታኔን ለማጥፋት የተለያዩ ዘዴዎችን በመጠቀም ላይ የሚገኝ ሲሆን ይህም የከፋ ውጤት አስከትሏል።
የጋዜጠኞች መብት ተከራካሪ የሆነው የኮሚቴ ቱ ፕሮቴክት ጆርናሊስትስ (Committee to protect Journalists) መረጃ እና የሂዩማን ራይትስ ዎች ጥናት እንደሚያመለክተው ኢትዮጵያ ከኢራን በመቀጠል በዓለም ላይ በርካታ ቁጥር ያላቸው ጋዜጠኞችን ለስደት የምትዳርግ ሀገር ሆናለች። የመንግስት አካላት አፋኝ ህጎችን መሰረት አድርገው ጋዜጠኞች በየወቅቱ ያሉ ክስተቶችን እና ጉዳዮችን አስመልከተው በሚሰሩት ዘገባ እና ትንታኔ ምክንያት በተደጋጋሚ ክስ ይመሰርቱባቸዋል፤ ፍርድ ቤቶችም ክሱን ተከትለው የጥፋተኝነት ውሳኔ ያስተላልፋሉ፡፡ በአሁኑ ወቅት እስክንድር ነጋን እና ርዕዮት ዓለሙን የመሰሉ ግለሰቦች በአዲስ አበባ እና በክልሎች የሚገኙ ተለይተው የሚታወቁም ሆነ የማይታወቁ ከደርዘን በላይ የሚሆኑ ጋዜጠኞች እየደረሰባቸው የሚገኘውን ፈተና የሚያሳዩ ምልክቶች ሆነዋል። ጋዜጠኞቹ በርካታ ስጋት ውስጥ የሚገኙ፣ ማስፈራሪያ የሚደርሳቸው፣ አልፎ አልፎም አካላዊ ጥቃት የሚፈጸምባቸው እና ፖለቲካዊ ይዘት ያለው የወንጀል ወይንም የሽብር ክስ የተመሰረተባቸው ናቸው፡፡ የፍርድ ቤት ክርክራቸው ፍትሃዊ የፍርድ ሂደትን የሚጥሱ አሰራሮች የሚታዩበት ሲሆን ፍርድ ቤቶቹም በያዟቸው ጉዳዮች ላይ የሚሰጧቸው ውሳኔዎች ገለልተኛ እንዳልሆኑ የሚያሳይ ነው።
በኢትዮጵያ የሚገኙት አብዛኛዎቹ የህትመት መገናኛ-ብዙሃን ከመግስት ጋር የቀረበ ትስስር አላቸው፤ በወሳኝ ጉዳዮች ላይ ከመንግሰት የተለየ አቋም እምብዛም አያንጸባርቁም።የግል የህትመት መገናኛ-ብዙሃን በርካታ ከቁጥጥር ጋር የተያያዙ ችግሮች ያጋጥማቸዋል እንዲሁም በደህንነት ሰራተኞች ተከታታይ ወከባ ይደርስባቸዋል፡፡ መንግስትን የሚተቹ የህትመት ውጤቶች በየጊዜው ይዘጋሉ፣ የበሰለ ትችት የሚያቀርቡ የህትመት ውጤቶችን የሚያትሙ እና የሚያከፋፍሉ አሳታሚዎች እና አከፋፋዮችም ተዘግተዋል፡፡ የመንግስት ፖሊሲዎች ላይ ትችት የሚሰነዝሩ ጋዜጠኞች እና የቤተሰብ አባሎቻቸው ጭምር የጥቃት፣ የመታሰር እና የገቢ ምንጫቸውን የማጣት ዘላቂ ስጋት ላይ ይወድቃሉ፡፡ መንግስት አብዛኛውን የመገናኛ-ብዙሃን ተቆጣጥሮ የሚገኝ ሲሆን የቀሩት ጥቂት የግል መገናኛ-ብዙሃንም በተለይ ለአሳሳቢ የፖለቲካ ጉዳዮች ላይ በሚሰጡት ሽፋን ራሳቸው ላይ ቅድመ ምርመራ የሚያደርጉ ያደርጋሉ ይህም እንዘጋለን ከሚል ፍርሃት የመነጨ ነው፡፡
ይህ ሪፖርት የኢትዮጵያ መንግስት ነጻ ጋዜጠኝነትን እና ትንታኔን ለመቆጣጠር እንዲሁም መረጃ የማግኛ መንገድን ለመገደብ የተጠቀማቸውን ዘዴዎች የሚዘግብ ነው፡፡ ሪፖርቱ ከ70 የሚበልጡ የአሁን እና የቀድሞ ጋዜጠኞችን እና የመገናኛ-ብዙሃን ባለሙያዎችን ቃለ-መጠይቅ በማድረግ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙሃን የሚገኝበትን አስከፊ ሁኔታ እና በዚህም ምክንያት ሃሳብን በመግለጽ ነጻነት እና መገናኛ-ብዙሃን ላይ የደረሰውን አሉታዊ ተጽዕኖ ይዘረዝራል፡፡
በስፋት በተዘገቡ ጉዳዮች ላይ ከዓለምዓቀፍ ማህበረሰብ የተሰነዘሩ ውግዘቶች ቢኖሩም የኢትዮጵያ መንግስት ለገለልተኛ የመገናኛ-ብዙሃን ድምጽ ምንም አይነት የመለሳለስ ምልክት አላሳየም፤ እ.ኤ.አ. በ2014 ዓ.ም የግል መገናኛ ብዙሃን ላይ የሚደርሰው አሉታዊ ተጽዕኖ በእጅጉ ተባብሷል፡፡ አስር ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን ክስ የተመሰረተባቸው ጋዜጠኞችን ዝርዝር ተቀላቅለዋል እንዲሁም አምስት መጽሄቶች እና አንድ ጋዜጣ በመንግስት የዛቻ እና የማስፈራሪያ ዘመቻ ከተካሄደባቸው በኋላ እንዲዘጉ ተደርጓል፡፡ ዘመቻው በመንግስት በሚተዳደረው የቴሌቪዥን ጣቢያ የህትመት ውጤቶቹ ሽብርን እንደሚደግፉ አስመስሎ ማቅረብ፣ የህትመት ውጤቶቹን የሚያትሙ ማተሚያ ቤቶችን ማዋከብ፣ በህትመት ውጤቶቹ የማከፋፈል ስራ ላይ የመንግስት ጣልቃ ገብነት፤ እንዲሁም ከደህንነት ባለስልጣናት በርካታ ዛቻዎችን መሰንዘርን ያካትታል፡፡ ይህም በመጨረሻ በደርዘን የሚቆጠሩ ጋዜጠኞች እና በርካታ የህትመት ውጤቶች ባለቤቶች ሃገር ለቀው እንዲሰደዱ እና ባለቤቶቹ የወንጀል ክስ እንዲመሰረትባቸው በማድረግ ተከናወኗል። ፍርድ ቤቶች ሌላ ምንም አይነት ተጨባጭ ማስረጃ ሳይቀርብ መንግስትን የሚተቹ ጽሁፎችን ብቻ መሰረት በማድረግ በሶስት የህትመት ባለቤቶች ላይ በሌሉበት እያንዳንዳቸው ከሶስት አመት የሚበልጥ እስር እንዲቀጡ ወስነውባቸዋል፡፡ የሌሎች የህትመት ባለቤቶች ክስም በሂደት ላይ ነው፡ ፡
መንግስት ከሚፈፅማቸው ትኩረትን የሚስቡ እስሮች በተጨማሪ መገናኛ-ብዙሃንን ለማዳከም እና ለመዝጋት ሌሎች በርካታ በግልጽ የማይታዩ የእጅ አዙር መንገዶችን ይጠቀማል፡፡ የደህንነት ሰራተኞች በአሳሳቢ የፖለቲካ ጉዳዮች ዙሪያ የሚጽፉ ጋዜጠኞች ላይ ተከታታይ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ያደርሱባቸዋል፡፡ እነዚህ ዛቻዎች ብዙውን ጊዜ ከጋዜጠኞቹም አልፎ ወደ ቤተሰባቸው እና ጓደኞቻቸው ድረስ ይዘልቃሉ፡፡ የሚደርስባቸውን ማስፈራሪያ ተቀብለው በሚሰሩት ዘገባ ላይ ቅድመ-ምርመራ የማያካሂዱት በአብዛኛው ክስም ሳይመሰረትባቸው በዘፈቀደ ይታሰራሉ እንዲሁም ተጨማሪ ዛቻ እና ማስፈራሪያ ይደርሳቸዋል፡፡ ከአዲስ አበባ ውጭ በሚገኙ አካባቢዎች በጋዜጠኞች ላይ የሚደርሰው ያልተገባ አያያዝ እና ድብደባ የተለመደ ሆኗል፤ በአብዛኛው ጊዜም የወነጀል ክስ ተከትሎ ይመጣል። ብዙዎቹ ለረዥም ጊዜ ያገለገሉ የግል ጋዜጠኞች በርካታ ጊዜያት እስር ተፈጽሞባቸዋል፤ እንዲሁም ከደህንነት ባለስልጣናት፣ ከገዢው ፓርቲ ካድሬዎች፣ እና ከቀድሞው የኢትዮጵያ ማስታወቂያ ሚኒስቴር አሁን ደግሞ የመንግስት ኮምዩኒኬይሽን ጉዳዮች ቢሮ ከተባለው መስሪያቤት ባለስልጣናት በመቶዎች የሚቆጠሩ ዛቻዎችን ተቀብለዋል፡፡
ይህም በመጨረሻ ላይ የኢትዮጵያ ጋዜጠኞች በራሳቸው ላይ ቅድመ-ምርመራ በማድረግ የገዥውን ፓርቲ አጀንዳ ከማራገብ ወይንም ራሳቸውን እና ቤተሰባቸውን አደጋ ላይ ሊጥል የሚችል ዘገባ እና እና ትንታኔ ማቅረብ ከመቀጠል አንዱን የመምረጥ ከባድ ፈተና ውስጥ እንዲወድቁ ያደርጋል።
በግለሰብ ጋዜጠኞች ላይ ከሚደርሰው ጥቃት በተጨማሪ የግል መገናኛ-ብዙሃን ባለቤቶች የህትመት ውጤቶቻቸውን የሚያሳትሙባቸውን ማተሚያ ቤቶች ለማዳከም ባለስልጣናቱ የተለያዩ መንገዶችን ይጠቀማሉ፡፡ በመግስት ስር የሚተዳደረው እና በመደበኛነት ጋዜጦችን የማተም አቅም ያለው ብቸኛ ማተሚያ ቤት የግል ህትመት ውጤቶችን ስራ ያዘገያል ወይንም አይቀበልም፣ በአንድ አጋጣሚ መንግስት በጣም አሳሳቢ ነው ባለው ጉዳይ ላይ ዘገባ ያሳተመን ጋዜጣ 40,000 ኮፒ ህትመት አቃጥሏል፡፡ የደህንነት ሰዎች የግል ህትመት ውጤቶች አከፋፋዮች ላይም የሚያደርጉትን ክትትል እና የሚያደርሱትን ጥቃት ጨምረዋል፡፡ የጋዜጠኞች የመረጃ ምንጮች በተደጋጋሚ ለጥቃት እየተጋለጡ ከመገናኛ ብዙሃን ጋር ለመነጋገር ፍርሃት የሚያድርባቸው ሰዎች ቁጥርም እየጨመረ ነው።
መንግስት የግል ጋዜጠኞች ማህበር ለማደራጀት የሚደረግን ሙከራ ያግዳል እንዲሁም የግል የህትመት ውጤቶች ያላቸውን ፖለቲካዊ ትስስር በተመለከተ የደህንነት ባለስልጣናት ሰፊ የኋላ ታሪክ ጥናት ያካሂዳሉ፡፡ የመንግስት ወይም የገዥው ፓርቲ ሙሉ ደጋፊ ያልሆኑ የግል ህትመቶች ለሚያቀርቡት የህትመት ፈቃድ አሊያም እድሳት ጥያቄ ባለስልጣናት ምላሽ ለመስጠት ይዘገያሉ፡፡
የድረ-ገጽ መገናኛ ብዙሃንም በተሻለ መልኩ የተያዙ አይደሉም፡፡ በውጭ ሃገራት በሚኖሩ ኢትዮጵያዊያን የሚመሩ በርካታ ጦማሮች እና ድረ-ገጾች ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳይታዩ ተደርገዋል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2014 ዓ.ም ዞን ዘጠኝ በመባል የሚታወቁት በሃገሪቱ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ትንታኔ የሚያቀርቡ የጦማሪያን ስብስብ 80 ቀናት ክስ ሳይመሰረትባቸው በእስር ከቆዩ በኋላ በጸረ-ሽብር አዋጁ እና የወንጀል ህጉ መሰረት ተከሰዋል፡፡ በቀረበው ክስ መሰረት በክስ ዝርዝር ሰነዱ ከተጠቀሰባቸው ማስረጃ መካከል አንዱ ቴክኒካል ቴክኖሎጂ ኮሌክቲቭ በተባለው በኢንተርኔት ላይ የሚገኝ የግላዊ መረጃዎችን ሚስጥራዊነት ለመጠበቅ የሚረዱ ተግባራትን እና መሳሪያዎችን በሚያቀርበው ዓለም ዓቀፍ መንግስታዊ ያልሆነ ድርጅት የዲጂታል ደህንነት ጥበቃ ስልጠና ወስደዋል የሚል ነው፡ ፡ የዞን ዘጠኝ አባላት መታሰር እና መከሰስ በሃገሪቱ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት ላይ የፍርሃት ድባብ ፈጥሮአል። ይህም ጦማሪዎች እና የኢንተርኔት ላይ ተሟጋቾች በፌስቡክና በመሳሰሉ እና ሌሎች ማህበራዊ ድረ-ገጾች በሚለጥፏቸው ትችቶች ምክንያት ችግር ውስጥ ልንገባ እንችላለን የሚለውን ስጋታቸውን በእጅጉ ከፍ አድርጎታል፡ ፡
በሬድዮ እና ቴሌቪዥን ስርጭት ላይ ያለውም ሁኔታ ተመሳሳይ ነው፡፡ አብዛኛዎቹ የሃገሪቱ ሬድዮ እና ቴሌቪዥን ጣቢያዎች በመንግስት ስር የሚገኙ ሲሆን ገለልተኛ የዜና ዘገባ እና ትንታኔ አይቀርብባቸውም፡፡ ከ80 በመቶ የሚበልጠው የኢትዮጵያ ህዝብ የሚኖረው በገጠራማ አካባቢዎች በመሆኑ እና ሬድዮ እስከአሁን ዋናው የዜና እና መረጃ ማግኛ ምንጭ ከመሆኑ አንጻር ይህ በጣም አሳሳቢ ጉዳይ ነው፡፡ በፖለቲካዊ ጉዳዮች ላይ ዘገባ የሚያቀርቡ ጥቂት የግል ሬድዮ ጣቢያዎች ዝግጅቶቻቸውን አየር ላይ ከማስተላለፋቸው ከቀናት በፊት የመንግስት ባለስልጣናት እንደሚገመግሙት እና እንደሚያጸድቁት ለሂውማን ራይትስ ወች ተናግረዋል፡፡ ተቀባይነት ካገኘው ይዘት የሚያፈነግጡ አሰራጮች በመንግስት ባለስልጣናተ የሚፈጸም እስር እና ወከባ ጋር መጋፈጥ ሊኖርባቸው ይችላል።
በርካታ ጋዜጠኞች ከማያቋርጥ የማዋከብ እና የፍርሃት ሕይወት ለመገላገል ሲሉ ከመንግስት ጋር ትስስር ባለው መገናኛ-ብዙሃን ተቀጥረው መስራት ይመርጣሉ፡፡ አንዳንዶች የመንግስት ባለስልጣናትን እስከማያስቆጣ ድረስ ባለው መለያ መስመር ላይ ሆነው ትችቶችን የሚያቀርቡ ሲሆን ሌሎች ደግሞ የመንግስትን የልማት ውጤቶች በማስተዋወቅ እና በማጋነን የመንግስት ፕሮፖጋንዳ አራጋቢዎች ሆነው ይሰራሉ፡፡ በእነዚህ መገናኛ ብዙሃን የኢህአዴግ አባልነት እድገት ለማግኘት የሚጠየቅ መስፈርት ነው፡፡
በኢጥዮጵያ የሚገኙት የውጭ መገናኛ ብዙሃን ውሱን ናቸው። የአሜሪካ ድምጽ ቮይስ ኦፍ አሜሪካ (ቪኦኤ) እና የጀርመን ድምጽ ዶቼቬሌ የቴሊቪዥን እና የሬድዮ ሽፋን በመስጠት በርካታ የዲያስፖራ ጣቢያዎችን ተቀላቅለዋል፡፡ ሆኖም የአየር ሞገዳቸውን በማገድ፣ በሰራተኞቻቸው እና የመረጃ ምንጮቻቸው ላይ ዛቻ እና ጥቃት በማድረስ እንዲሁም በቅርቡ ደግሞ የዲያስፖራ መሰረት ያላቸውን ስርጭቶች የሚመለከቱ እና የሚያዳምጡ ግለሶቦችን በማጥቃት እና በማሰር ጭምር መንግስት የሃገር ውስጥ ተከታታዮቻቸውን ለመገደብ የተለያዩ ዘዴዎችን ይጠቀማል፡፡
እ.ኤ.አ. ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ በበጎ አድራጎት ድርጅቶች እና ማሕበራት ላይ በደረሰው ጫና ምክንያት በርካታ የሲቪል ማሕበራት ስራ ለማቆም የተገደዱ ሲሆን ያሉት የፖለቲካ ፓርቲዎች ደግሞ ጥብቅ ገደብ ተጥሎባቸዋል፡፡ ይህ ደግሞ ንቁ እና ነጻ የመገናኛ-ብዙሃን ዘርፍ በመንግስት አስተዳደር ላይ ተሳትፎን ለማበርከት እና የሰብዓዊ መብቶች በተሻለ ሁኔታ እንዲከበሩ ለማገዝ ያለውን አስፈላጊነት የበለጠ ያጎላዋል። አለመታደል ሆኖ በፖለቲካ ሁነቶች ላይ ገለልተኛ ሽፋን እና የዜና ትንታኔ ለመስጠት ያለውም ጥቂት ክፍተት እ.ኤ.አ. በ2014 ዓ.ም. የበለጠ ተጣቧል፡፡ ከግንቦት 2007 ምርጫ መቃረብ ጋር በተያያዘ ኢትዮጵያዊያን የተለያዩ የፖለቲዊ አተያዮች እና ትንታኔዎችን የሚያገኙበት እድል እየተመናመነ ነው።
በኢትዮጵያ የሚገኙ መገናኛ-ብዙሃን ሁኔታን ለማሻሻል በአጭር እና በረጅም ጊዜ አሁንም ብዙ ሊደረግ ይችላል፡፡ እንደ መጀመሪያ እርምጃ መንግስት ክሶችን በአስቸኳይ በማንሳት የታሰሩ እና የተፈረደባቸው ጋዜጠኞች እና ጦማሪያንን ክስር ሊለቅ ይገባል፡፡ የኢትዮጵያ መሪዎች ንቁ እና ገለልተኛ የመገናኛ ብዙሃን መኖር ለሃገሪቱ እድገት አስተዋጽኦ እንደሚያበረክት ሊገነዘቡት ይገባል፡፡ እንዲሁም በመጪዎቹ ሳምንታት እና ወራት መንግስት የጸረ- ሽብር ህጉን ጨምሮ ሌሎች መገናኛ ብዙሃኑ ላይ አሉታዊ ተጽእኖ የሚያሳድሩ አፋኝ ህጎችን ማረም አለበት፡፡ የሚወጡ ህጎች እና የሚፈጸሙ ተግባራት የኢትዮጵያ ህገ-መንግስት እና ዓለምዓቀፍ መለኪያዎች ጋር በሚጣጠም መልኩ መሆኑን ባለስልጣናት ማረጋገጥ አለባቸው፡፡
ለኢትዮጵያ መንግስት
ምክረ ሃሳቦች

• ሁሉንም ክሶች በአስቸኳይ ማንሳት እንዲሁም በወንጀል መቅጫ ህጉ እና በጸረ-ሽብር አዋጁ መሰረት ተከሰው በዘፈቀደ የታሰሩ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን በሙሉ መፍታት።
• የጸረ-ሽብር አዋጁ እና የመገናኛ-ብዙሃን እና የመረጃ ነጻነት አዋጁ መሰረዝ አሊያም በኢትዮጵያ ህገ- መንግስት እንዲሁም በክልላዊ እና ዓለምዓቀፋዊ የሰብዓዊ መብት ህጎች ላይ ሃሳብን የመግለጽ ነጻነት መብት ከተቀመጡ መስፈርቶች ጋር በሚጣጣም መልኩ ከፍተኛ መሻሻያ ማደረግ፡፡
• የስም ማጥፋትን የወንጀል ቅጣት እንዲያስከትል ተደርጎ በወንጀል መቅጫ ህጉ አንቀጽ 613 ላይ የተደነገገውን ማሻሻል።
• በህትመት እና ብሮድካስት መገናኛ ብዙሃን ላይ መንግስት ያለውን የባለቤትነት ድርሻ መገደብ ፤ እንዲሁም የግል መገናኛ-ብዙሃን ባለቤትነትን የሚገድቡ ጉዳዮችን ለማስቀረት እና ገለልተኛ እና ንቁ መገናኛ-ብዙሃንን ለማበረታታት የሚያስችሉ የህግ እና የፖሊሲ ማስተካከያ እርምጃዎችን መውሰድ።
• አዳዲስ የህትመት እና የሬድዮ ስርጭቶች ቁጥጥርና ፈቃድ አሰራር ቀልጣፋ ማድረግ እና ከፖለቲካዊ ይዘት ነጻ ማድረግ። ቁጥጥር አድራጊ ባለስልጣን አካላት ገለልተኛ መሆን አለባቸው፤ እንዲሁም አስተዳደራዊ እና ተግባራዊ እንቅስቃሴያቸው ከመንግስት የደህንነት አካላት አና ከመንግስት ኮምዩኒኬይሽን ጉዳች ቢሮ መለየት አለበት፡፡
• የኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለስልጣን ገለልተኛነትን ለማረጋገጥ ማሻሻያዎች ማድረግ።
• የሃገር ውስጥ እና የውጭ ጋዜጠኞች በመላው ሃገሪቱ በነፃነት የመንቀሳቀስ መብታቸውን የሚገድቡ አሰራሮችን ማስወገድ፣ ይህም ከፍተኛ የሰብዓዊ መብት ጥሰት እየተፈጸመባቸው ይገኛሉ በሚባሉ አካባቢዎች በነጸነት መንቀሳቀስን እንዲጨምር፣ ፖሊስ እና የደህንነት ሰዎች መገናኛ-ብዙሃን በነጻነት ይንቀሳቀሱ ዘንድ ፈቃድ እንዲሰጡ መመሪያ መስጠት፤ በዛቻ፣ በማስፈራራት እና በማሰር የጋዜጠኞችን እንቅስቃሴ የገደበ ማንኛውም ፖሊስ በያዘው የማዕረግ እርከን ልዩነት ሳይደረግ መቅጣት።
• የፖለቲካ ፓርቲ ፣ የመገናኛ ብዙሃን እና የጦማሪያን ድረ-ገጾችን ማፈን እና ቅድመ ምርመራ ማድረግን ማቆም እንዲሁም ለወደፊት እንደዚህ አይነት ድረ-ገፆችን ላለማፈን በይፋ ቃል መግባት።
• የሬድዮ እና የቴሌቪዥን አየር ሞገዶችን ማፈን ማቆም ፤ ለወደፊቱም የሬድዮ እና ቴሌቪዥን አየር ሞገዶችን ላለማፈን በይፋ ቃል መግባት።
• አስተያየት የመስጠት እና ሃሳብን የመግለጽ ነፃነት መብቶችን ለማዳበር እና ለመጠበቅ የሚንቀሳቀሰው የተባበሩት መንግስታት ልዩ ራፖርተር ኢትዮጵያን እንዲጎበኝ እና የግል የህትመት እና የብሮድካስት መገናኛ-ብዙሃን ያሉበትን ሁኔታ እንዲገመግም እንዲሁም በእስር ላይ የሚገኙ ጋዜጠኞችን ሁኔታ እንዲያጠና ግብዣ ማቅረብ።
የአውሮፓ ህብረት አባል ሃገራት እና ዩናይትድ ስቴትስን ጨምሮ ለዓለምዓቀፍ የኢትዮጵያ ለጋሾች
• በዘፈቀደ የታሰሩ እና በወንጀል ህጉ እና በጸረ-ሽብር አዋጁ መሰረት የተከሰሱ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን በሙሉ እንዲፈቱ በይፋ ጥሪ ማቅረብ አና በተናጥል ጫና ማሳደር።
• የጋዜጠኞች የፍርድ ቤት ክርክር ሂደት ዓለምዓቀፍ የፍርድ ሂደት መስፈርቶችን ያሟላ መሆኑን ለማረጋገጥ የፍርድ ሂደት ክትትሉን ማሻሻል እና መጨመር።
• የታሰሩ ጋዜጠኞች እና ጦማሪያን የሚገኙበትን ሁኔታ ለመገምገም እስር ቤቶችን እና ማቆያ ጣቢያዎችን ለመጎብኘት ጥያቄ ማቅረብ።
• ሃሳብን የመግለጽ ነፃነትን የተመለከቱ አሳሳቢ ጉዳዮች እና የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ልማትን እና ደህንነትን እንደሚጎዱ ያላቸውን ስጋት ለመንግስት ባለስልጣናት በይፋ እና በግል መግለፅ።
• ገለልተኛ የጋዜጠኝነት ማህበር የሚፈጠርበትን መንገድ ጨምሮ የኢትዮጵያ መገናኛ-ብዙሃን የሙያ ብቃት እንዲዳብር ድጋፍ ማበርከት፤ ከአዲስ አበባ ውጭ ለሚገኙ ለግል መገናኛ-ብዙሃን ጋዜጠኞች የተለዩ እድሎች መኖራቸውን ማረጋገጥ እና የመገናኛ-ብዙሃን አቅምን ለማሳደግ ያለሙ እንቅስቃሴዎች እንዲካተቱ ልዩ ጥረት ማድረግ።
• ነጻ ጋዜጦች እና ሌላ አይነት ህትመቶች መንግስታዊ ያልሆኑ ወይም በመንግስት ቁጥጥር ስር ያልገቡ ማተሚያ መሳሪያዎችን የሚያገኙበትን መንገድ ለማመቻቸት ድጋፍ ማድረግ።
በመንግስት ለተያዙ እና ከመንግስት ጋር ትስስር ላላቸው ማተሚያ ቤቶች
• ከመንግስት ጋር የተለየ ትስስር ያላቸው ህትመቶች ከሚታተሙበት የጊዜ ሰሌዳ በሚጣጠም መልኩ ሁሉንም ፈቃድ ያላቸው የግል መገናኛ ብዙሃን ህትመቶችን በተገቢው የጊዜ ገደብ እና አግባብ ባለው ሁኔታ በገለልተኝነት ማተም።
በኢትዮጵያ ውስጥ ለሚገኙ የውጭ ሬድዮ እና ቴሌቪዥን አስተላላፊዎች
• የተለየ አደጋ ያለባቸውን የመረጃ ምንጮች ለመለየት የሚጠቀሙበትን አሰራር ማጠናከር እና አደጋውን ለመቀነስ የሚወስዱትን እርምጃ ማዳበር፤ ይህም የግለሰቡ ማንነት እንዳይታወቅ ማድረግ፣ ማንነታቸውን በተመለከተ ያላቸውን መረጃ ሚስጥራዊ አድርጎ ማስቀመጥ እና ከፍተኛ ታዋቂነት ላላቸው ግለሰቦች ያለውን አደጋ እንዲገነዘቡት ማድረግን ይጨምራል፡፡
ለኬንያ፣ ደቡብ ሱዳን እና ዩጋንዳ መንግስታት
• ጋዜጠኞች እና ሌሎች የመገናኛ ብዙሃን ባለሙያዎችን ጨምሮ ጥገኝነት ጠያቂዎች ለጥገኝነት ማመልከቻቸው በአፋጣኝ ምላሽ መስጠት እና ሊደርስባቸው ከሚችለው ጥቃት ከለላ እንደተሰጣቸው ማረጋገጥ።
source Zehabesha